"ይቺ ሀገር ውለታ ለዋለላት አትሆንም" ይላል። ይሄን ሲል ሰምተው ለሀገርህ የሰራኸው ውለታ ምንድን ነው? ብለው ሲጠይቁት፦
"ለናት ሀገር ጥሪ ዘምቼ ነበር። ሚንስ ቤት እንጨት ፈላጭ ነበርኩ።"ብሎ ሲመልስ አፉን እንኳን ሀፍረት ጥቂት ያዝ አያደርገውም። ማድቤት ለማድቤት ሲንፏቀቅ የከረመ እንኳን ዛሬ ለኑሮው መናጋት የሚወቅሰው ሀገሩን ነው። ሀገር መስደብ እና መውቀስ ለስንፍና ማባበያ የሚሆንበት ዘመን ላይ ደርሼ ይህን አያለው ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር።
እኔ ከጀብሃ መንጋጋ ስንቴ ያመለጥኩ፣ ዳር ድንበር ላይ ደረቴን ለጥይት ሰጥቼ የተጋደልኩ ሻለቃ የነበርኩት እንኳን፣ ዛሬ እንጀራዬ ሆኖ ማዕረግ በደረደርኩበት ትከሻዬ አመድ ብሸከምም፣ ሀገሬን ግን 'ውለታ ቢስ ነች' ለማለት አልደፍርም። ሀገር ሁሌም እንደ እናት ነች። ይልቅ እኔ የሚሰማኝ በደግ እናቱ ቤት ክፉ እንጀራ አባቶች በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥሙት እድለ ቢስ ልጅ አይነት ነው። ለዚህም ደግ እናቴን በጭራሽ አልወቅስም።