ዋናው መግቢያ በር ላይ ስንደርስ ሰውነታቸው ፈርጣማ በቁጥር አራት የሆኑ ወጣት የግብጽ ወታደሮች ተቀበሉንና እንደ አመጣጣችን አሰልፈው ሻንጣችንንና ኪሳችንን እነሱ ካሉበት አጥር ከመግባታችን በፊት ፈተሹን። ዓይኔን ወደ ተራራው ላክው ራቅ ራቅ ብለው የተወሰኑ የግብጽ መለዮ ያለበት የወታደር ልብስ የለበሱ ሰዎች መሳሪያ ወድረው አካባቢውን እየጠበቁ እንዳሉ አስተዋልኩ። ወታደሮቹ ሰላማዊ መሆናችንን ሲያረጋግጡ አሳለፉን። ጉዞችንን ወደ ግቢው አደረግን።
ከወታደሮቹ ትንሽ እንደራቅን ሶስት መነኩሴዎች እንደገና ከግቢው በር ወጥተው ተቀበሉን። በመምጣታችን ደስታ ቢታይባቸውም ሁሉንም ሰው ከወዴት እንደመጣ መጠየቅ ስለነበረባቸው የመጣንበትን ቦታ፣ ሀይማኖታችንን፣ የመጣንበትን ምክንያት፣ ፓስፖርትና ሌሎችን ነገሮች አከታትለው ጠየቁን። አባ እና እኔ እንደ ባህላችን ታላላቅ ገዳማት ስንሄድ እንደምናደርገው ጫማችንን አውልቀን በፌስታል አድርገን በእጃችን ያዝን። ሌሎቹ ግን ጫማቸውን ከእግራቸው ሳያወልቁ ግቢው ውስጥ ገቡ።
እንደገባን ከተሳለምንና ለጸሎት ፋታ ከወሰድን በኃላ እዚህ ግቢ ውስጥ በግንብ ከተሰራ የላሜራ ክዳን ያለው ማረፊያ ስር ተጠለልን። አሁን ከሀገር ቤት ፈልጌያቸው የመጣሁትን ኢትዮጽያዊ መነኩሴ አባ ሰላመ አብን አባ ሳሙኤል እንዴት እንደሚያገናኙኝ እያሰብኩ ነው። እስከ አሁን የተወሰኑ መነኮሳትን አትክልቱ ስፍራ ላይና ግቢው ውስጥ ተመልክቼ ነበር ከመካከላቸው ግን አንድም ኢትዮጵያዊ አባት አላየሁም።...