ETB A
13 hours ago
በአጎራባቿ ሠራባ ከተማ ምዕራብ በኩል መቶ ሜትር ወጣ ብዬ ዋልድባ ጫፍ ላይ ቆሜያለሁ። ረፋድ ሆኖል። መምህሩ አሁንም አጠገቤ ድንዛዜዬ ያስጨነቀው መስሎ በጸጥታ ተገትሯል። ሠራባ ልክ እነደ እረኛ ጋሜ የተራራ ጫፍ ላይ ጉች ያለች እንደነገሩ ከተማ ነች። ከጀርባዬ አንድ ክፍለ ጦር የወታደር ካምፕ ሰፎሯል። ከአዲስ አበባ ካርቱም የሚዘልቀው መንገድ ከተማዋን ለሁለት ከፍሎ የወታደር ካምፑን ወደ ግራ ትቶ ወደ እልፍ ይጉዳል።
ማየት እስከምችለው ጥግ መንገዱን ተከተልኩት።
ዓይኖቼን እያንከራተትኩ ዙሪያ ገባውን ለመቃኘት ሞከርኩ እዚያ ማዶ በሰሜን በኩል አይደፈሬዎቹ የወልቃይት ምድር ሰልፈኛ ተራሮች ስትር ብለዋል። አሰላለፋቸው የሆነ ተጠንቀቅ ነገር አለበት። በላያቸው ላይ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረ ሰጋር የበልግ ንፋስ በማናለብኝነት ይጋልባል። በግራዬ በኩል እስከ አድማሱ ጥግ ተንጣሎ የሚታየኝ የቋራ ምድር ነው።በመካከል የዮሐንሱ መተማ አርምሞን ተከናንቦ ተዘርግቷል።
መምህሩ ሹክክ ብሎ ተጠግቶኝ አለኝ...
"ሆይ ሆይ... እመትዋ ሠራባን መቶ ሜትር አልፈው ዋልድባን ተረገጡ ማቆልቆል ነው።"
አዎ መተማን፣ ካርቱምን፣ ሱዳንን፣ ካይሮን፣ ምናልባት ባቢሎልንን ኹሉ አልፎ የሚሄድ ዘላለም የሚመስል ቁልቁለት የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው።...